የብሄሮች ግንባር ወይስ ህብረብሄራዊ ድርጅት⁉️  by Gebreselase

የብሄሮች ግንባር ወይስ ህብረብሄራዊ ድርጅት⁉️

——————————————-

 

ከኢህኣዴግ በተፃራሪ መንገድ የቆሙት የፖለቲካ ሃይሎች ኢህኣዴግ ከግንባርነት ፈርሶ ወደ ኣንድ ውሁድ ፓርቲ መለወጥ ኣለበት፥ ክልሎችም በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ እና ማንነት መከለል የለባቸውም እያሉ ቆይተዋል። ይህ ኣስተሳሰብ የሚቀነቀነው ብዙሃነትን በማይቀበሉ ሃሳዊያኑ የኣንድነት ሃይሎች ሲሆን ኢህኣዴግ ውስጥ ባሉት ወኪሎቻቸው ኣማካኝነትም ከግንባር ወደ ውሁድ ፓርቲ የሚለውን ሃሳብ ወደ ኢህኣዴግ ውስጥ ገብቶ በባህርዳሩ ስብሰባ ላይ መነሳቱ ኣልቀረም። እንደዚህ ኣይነት ሃሳብ የሚያነሱ ሃይሎች ኣገሪቷ በተወሃደ ህብረብሄራዊ ፓርቲ እንድትመራ ካላቸው መልካም ምኞት የመነጨ ሳይሆን በዋናነት ብዙሃነትን ካለመቀበልና ብሄርን መሰረት ኣድርገው የቆሙት የፖለቲካ ድርጅቶችን ህልውና ላማክሰም የታሰበ ዘዴ ነው። ይህ ደግሞ ወዴት እንደሚያመራ መገመት ኣይከብድም።

 

በኣጭሩ የድርጅቶቹ ህልውና በማክሰም በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ እና ማንነት የተዋቀሩት ክልሎችም በመልክኣ-ምድር እንዲከለሉ መጠየቁ ኣይቀሬ ይሆናል። ይህ ማለት ድግሞ በቀጥታ በብሄር የተደራጁት የፖለቲካ ድርጅቶችን ህልውና ብቻ ሳይሆን በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድ ላይ የተመሰረቱት የክልሎች ህልውናም የሚፈታተን ነው። በኣጭሩ ህገመንግስቱና ፌደራላዊ ስርኣቱ ተጥሶ ጉዞ ወደ ኣሃዳዊ ስርኣት መመልስ ይሆናል። በዚህ ወቅት የክልሎቹ ምላሽ ዝምታ እንደማይሆን ግልፅ ነው። በነገራችን ላይ ማእከላዊው መንግስት በሕገ መንግስት የጸደቀ የክልሎች ስልጣንን መቀነስ፣ ማስቀረትና ከዚያ በላይ ስልጣን መጨመር አይችልም። ብውህደት ስም ከየብሄሩ ጥቂት ሊሂቃን ወደ ስልጣን በማምጣትም የሚሸወድ ህዝብ ከእንግዲህ ወዲህ ስለማይኖር የኢትዮጵያ ፖለቲካ እስኪሰለጥን ድረስ በብሄር የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ ክልሎች መነካካቱ ቢቀር ይመረጣል። እንደ ቤልጄም የመሰለ ደልዳላ ህገመንግስታዊ ስርኣት የፈጠረ ኣገርም እስከ ኣሁን በብሄር የተደራጁ ፓርቲዎች ናቸው ያሏት።

 

በጠቅላይ ኣግላይ ፖለቲካና በዘረኝነት የተመረዘ ሊሂቅ እያለን፣ የስልጣን ፍላጎቱ ለማርካት ሲል ኣንዱን ብሄር በሌላኛው የሚያስነሳ ሊሂቅ እያለን፣ ብክልሉ የሚኖሩ የሌላ ብሄር ተወላጆች ላይ እስክ የጅምላ ግድያ የሚደርስ ጥቃት የሚፈጽም/የሚያስፈፅም ፖለቲከኛ ባለባት ኢትዮጵያ ያሉን እና የቀሩን ኣማራጮች ተከባብሮ መኖር ወይ መበታተን ብቻ እንደሆነ እስክንማር ድረስ ኣሁን ያለውን ድርጅታዊ ህልውና እና ህገመንግስታዊ ስርኣት መነካካት ኣስፈላጊ ኣይሆንም። ለማስታወስ ያክል፣ በህገመንግስቱ ኣይን ያነሰ የህዝብ ቁጥር ያላቸው የሃረሪና የጋምቤላ ክልሎች ብዙ የህዝብ ቁጥር ካላቸው የኦሮሚያ እና የኣማራ ክልሎች በኣገራዊ ጉዳይና እጣ ፈንታ በሚመለከት እኩል የፖለቲካ ስልጣን እና ወሳኝነት ኣላቸው።

 

በመሆኑም ይህ በህዝቦች መስዋእትነት የተገኘው ህገመንግስታዊ ስልጣን በምንም ኣይነት መልኩ ሊሸራረፍ ኣይገባም። እንዲያውም ቢቻል ቢቻል ኢህኣዴግ ያወጣውን ፖሊሲ በክልላቸው እያስፈጸሙ ያሉትን ኣምስት ኣጋር ድርጅቶች ወደ ኢህኣዴግ በኣባልነት ኣስገብቶ በኣገራዊ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ከፍ በማድረግ የራሳቸውን ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ዕድል ቢፈጥር ትክክለኛ እርምጃ ይሆናል። እንደሚታወቀው የኢህኣዴግን ፖሊሲ በማስፈጸም ኣንደኛ የወጣው የሱማሌ ክልልን እያስተዳደረ ያለውን በኣቶ ኣብዲ የሚመራው ድርጅት መሆኑን ይታወቃል። እነዚህን ትቶ ኢህኣዴግን ለመናድ ቀን ተሌሊት እየተጉ ያሉትን የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች ማስታመም ተገቢ ኣይደልም። ስለሆነም ኢህኣዴግ የማያዛልቀውን የውህደት እበደት ትቶ ለኣጋር ድርጅቶች በሩን ክፍት በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን ኣስፍቶ ጨዋታውን ሞቅሞቅ ያድርግ እንላለን። ይታሰብበት።

 

ላዕሌሁ ሰላም!

Comments

comments