የወባ በሽታን በትንፋሽ መመርመር የሚያስችል መሳሪያ ተሰራ

የወባ በሽታን በትንፋሽ ብቻ መመርመር የሚያስችል መሳሪያ መስራታቸውን የአሜሪካ ተመራማሪዎች አስታወቁ።

የወባ በሽታን በትንፋሽ መመርመር የመያስችለውን መሳሪያም ወደ አፍሪካ ሀገራት በማምጣት የተሳካ ሙከራ ማድረጋቸውን ነው ተመራማሪዎቹ ያስታወቁት።

መመርመሪያው በተለይም የወባ በሽታን በህፃናት ለይ ቀድሞ ለመለየት የሚያስችል መሆኑ ተረጋግጧል የሚሉት ተመራማሪዎቹ፥ መሳሪያው በብዛት ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ እሁንም ቀሪ ስራዎች አሉ ይላሉ።

መሳሪያው ስድስት አይነት የተለያዩ ጠረኖችን የመለየት አቅም ያለው ሲሆን፥ ይህም በሰዎች ውስጥ የወባ በሽታ መኖር አለመኖሩን ለመለየት የሚያስችለው መሆኑ ተነግሯል።

ተመራማሪዎቹ በወባ በሽታ የተጠቁ እና ያልተጠቁ 35 የማላዊ ህጻናት ላይ በመሳሪያው አማካኝነት ሙከራ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

በዚህም የትንፋሽ መመርመሪያ መሳሪያው የ29 ህጻናትን ትክከልኛ ውጤት ሰጥቷል የተባለ ሲሆን፥ ይህም 83 በመቶ ስኬታማ መሆኑን ያሳያል ይላሉ ተመራማሪዎቹ።

በአሁኑ ጊዜ የወባ በሽታን ለመመርመር ፈጣን የደም ምርመራ ዘዴ ጥቅም ላይ እየዋለ ሲሆን፥ ሆኖም ግን እነዚህ መመርመሪያዎች ውስንነት አላቸው ይላሉ የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች።

የደም ምርመራ ማድረግ ከዋጋ አንፃር ውድ መሆኑን እና በገጠራማ አካባቢዎች ደግሞ ቴክኒካዊ ባለሙያዎችን የማግኘት ፈተናዎች እንዳለውም ያነሳሉ።

አሁን ላይ የተገኘው የትንፋሽ መመርመሪያ ግን ምንም አይነት የደም ናሙና መውሰድ ሳያስፈልግ እና ያለ ቴክኒክ ባለሙያዎች ድጋፍ ሊካሄድ የሚችል በመሆኑ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ያነሳሉ።

Comments

comments