አትክልትና ፍራፍሬ አዘውትሮ መመገብ የልብ ድካም ታጋላጭነትን በ42 በመቶ ይቀንሳል-ጥናት

አትክልትና ፍራፍሬ መሰረት ያደረገ የአመጋገብ ስርዓት መከተል የልብ ድካምን በ42 በመቶ በመቀነስ ረጅም ዕድሜ ለመኖር እንደሚረዳ አንድ ጥናት አመላክቷል።

ተመራማሪወች አትክልት እና ፍራፍሬን አዘውትሮ መመገብ ሞትን ሊያስከትል ከሚችል የልብ ድካም ተጋላጭነትን ለመቀነስ ያግዛል ብለዋል።

ይህም በአምስት የተለያዩ የአመጋገብ ዓይነቶች የተካሄደው ጥናት እንደሚያመለክተው፥ አትክልት እና ፍራፍሬን አብዝቶ መመገብ በ42 በመቶ የልብ ድካም ተጋላጭነትን ይቀንሳል።

የልብ ድካም ልብ ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ደምን የመርጨት አቅሙ በሚዳከምበት ወቅት የሚከሰት ነው።

በኒውዮርክ በሚገኘው ኢካህን የህክምና ትምህርት ቤት ያሉት ተመራማሪዎች፥ በ15 ሺህ 569 ሰዎች ላይ ለአራት አመታት ያህል የአመጋገብና የጤንነት ሁኔታቸውን በተመለከተ ክትትል አድርገዋል።

የጥናቱ ታሳታፊዎችም ጥናቱ በተደረገበት ወቅት ስጋ እና የስጋ ተዋጽኦ፣ አትክልት፣ ጣፋጭ ምግቦች፣ እንቁላል እና ፍራሬዎች እንዲመገቡ ተደርጓል።

ተመራማሪዎችም የጥናቱ ተሳታፊዎች አመጋገብ ከልብ ድካም ጋር ያለውን ተያያዥነት አጥንተዋል።

በዚህም ተመራማሪዎቹ አትክልትን መሰረት ያደረገ አመጋገብ በሚከተሉ ተሳታፊዎች ላይ የልብ ድካም ህመም የመከሰቱ አጋጣሚ መቀነሱን አረጋግጠዋል።

ከዚህ በመነሳት ብዙውን ጊዜ አረንጓዴ ቅጠላማ ተክሎች፣ ፍራፍሬዎችን፣ ጥራጥሬዎችን እና ዓሳን መመገብ የልብ ድካም ተጋላጭነትን ለመቀነስ እንደሚረዳ ተመራማሪዎቹ መክረዋል።።

በሌላ በኩል የተቀነባበሩ የስጋ ውጤቶች፣ ቅባት የበዛባቸው ምግቦች፣ ከመጠን በላይ ካርቦ ሃይድሬት እና ስኳር የበዛባቸውን ምግቦች መመገብ የልብ ህመም ተጋላጭነትን ከፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም እነዚህን ምግቦች በተመጠነ መልኩ መውሰድ ይገባል ነው ያሉት።

Comments

comments