ብሪታኒያ ለውጭ ሀገር የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የምተሰጠውን ቪዛ በእጥፍ አሳደገች

ብሪታኒያ ለውጭ ሀገር ልዩ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የምተሰጠውን የቪዛ መጠን በእጥፍ አሳደገች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ከአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ውጭ የሚገኙ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ እውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ የቪዛ ቁጥሩ በእጥፍ እንዲጨምር ፈቅደዋል።

ይህም ብሪታኒያ ከአውሮፓ ህብረት አባልነቷ ከወጣች በኋላ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በዘርፉ የባለሙያ እጥረት ሊፈጠርባቸው እንደሚችል ግፊት ማሳደራቸውን ተከትሎ ነው ተግባራዊ የሆነው።

ሀገሪቱ የቴክኖሎጂውን ኢንዱስትሪ ለመደገፍ ሲባል በየዓመቱ ለውጭ ሀገር የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የሚሰጠው የቪዛ ቁጥር በዓመት ወደ 2 ሺህ እንዲጨምር ተወስኗል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሯ።

የቪዛ አገልግሎቱ የኮምፒውተር ፕሮግራም እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ባለሙያዎችን ያካተተ መሆኑም ተጠቁሟል።

ከዚህም ባሻገር የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ የ61 ሚሊየን ፓውንድ በጀትም በቀጣይ ዓመት ይፋ ይሆናል ተብሏል።

በዚህም ታዳጊዎችን ስለ ቀጥታ የኢንተርኔት ደህንነት ለማስተማር እና ሌሎች የቴክኖሎጂ ስራዎች እንደሚከናወኑ ነው የተጠቆመው።

ጠቅላይ ሚኒትር ሜይ የቴክኖሎጂ ዘርፉ የመንግስት የጀርባ አጥንት ነው ያሉ ሲሆን፥ በቀጣይም ኢንዱስትሪው ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል እንሰራለን ብለዋል።

በብሪታኒያ ለውጭ ሀገራት የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ቪዛ መስጠት የተጀመረው በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ዘመን በፈረንጆቹ በ2014 ነው።

Comments

comments