በ1 ዓመት ውስጥ የ18 ሀገራት ምርጫዎች በኢንተርኔት አማካኝነት ተጠልፈዋል- ጥናት

ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት በ18 የተለያዩ ሀገራት ውስጥ የተካሄዱ ምርጫዎች በኢንተርኔት አማካኝነት አሳሳች የሆኑ የምርጫ ዘመቻ መረጃዎች በመሰራጨት በምርጫዎቹ ላይ ጫና ማሳደራቸውን አዲስ የወጣ ጥናት አመልክቷል።

ፍሪደም ሀውስ የተባለ ኩባንያ ባጠናው ጥናት መንግስት እና በክፍያ አጀንዳ በሚፈጥሩ ሰዎች ኢንተርኔትን በመጠቀም በምን መልኩ ጫና እያሳደሩ ነው የሚለውን ተመልክቷል።

በዚህም 30 የዓለም መንግስታት የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጾችን ቸግባብ ባልሆነ መልኩ ለራሳቸው ዓላማ ማስፈጸሚያነት እየተጠቀሙት እንደሆነ የጥናቱ ሪፖርት አመልክቷል።

ሰዎች የሀሰት ዜናዎችን እንዴት መለየት እንደሚችሉ በማስተማር እና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ኔትዎርካቸውን የሚጠብቁበትን ስርዓት በመዘርጋት ኢንተርኔትን ካልተገባ ተግባር መጠበቅ ይቻላል ብሏል ሪፖርቱ።

ዓመታዊ ሪፖርቱ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ 65 ሀገራት የኢንተርኔት ነፃነት ላይም ጥናቱን ያካሄደ ሲሆን፥ ይህም የዓለምን የኢንተርኔት ኔትዎርክ ከሚጠቀሙት ውስጥ 87 በመቶ ያክሉን የሚያካልል ነው።

በዚህም የኢንተርኔት አጠቃቀም ነጻነት ከዓመት ዓመት እየቀነሰ መምጣቱንና ለዚህ ደግሞ መንግስታት ዜጎቻቸው በኢንተርኔት ላይ ምን እንሚጠቀሙ፣ ምን እንሚናገሩ እና ለጓደኞቻቸው የሚያካፍሉተን መከታተል በመጀመራቸው ነው ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም የመንግስት አካላት በምርጫ ወቅት የሚደረጉ ክርክርች ላይ በኢንተርኔት አማካኝነት ቁጥጥር ለማድረግ እና ጫና ለማሳደር እንደሚሞክሩም ፍሪደም ሀውስ በሪፖርቱ አመላክቷል።

እንዲህ አይነት ተግባርም ጥናቱን ካካሄደባቸው ሀገራት ውስጥ በ18 ሀገራት ላይ በስፋት መስተዋሉ ነው የተገለፀው።

በኢንተርኔት አማካኝነት በምርጫ ላይ ጫና የማሳደር ተግባርን በብዛት መንግስታት በራሳቸው ሀገር ውስጥ በሚደረጉ ምርጫዎች ላይ የሚፈፅሙት ሲሆን፥ አንዳንድ ሀገሮች ግን ከራሳቸው ሀገር አልፈው የሌሎች ሀገራት ምርጫ ላይ ጫና እየፈጠሩ መሆኑንም ተነግሯል።

ጥናቱ በዚህ ላይ ሩሲያ ትልቁን ድርሻ ትወስዳለች ያለ ሲሆን፥ በማሳያነትም ሀገሪቱ በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ በኢንተርኔት አማካኝነት የፈጠረችው ጫና አስቀምጧል።

Comments

comments