በሩሲያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ2018 የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ሃገራት ታውቀዋል

ከዓመታት የማጣሪያ ውድድሮች በኋላ በሩሲያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የ2018 የዓለም ዋንጫ የሚሳተፉ 32 ሀገራት ተለይተዋል።

አስተናጋጇ ሩሲያን ጨምሮ ለዓለም ዋንጫው ያለፉት ሀገራት የምድብ ድልድላቸውን በመጪው ታህሳስ 1 ቀን በሞስኮ የሚያውቁ ይሆናል።

ያለፉ ሀገራት ሙሉ ዝርዝር የሚከተለው ነው፤

ሩሲያ

በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ 65ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘውና የ2018 የዓለም ዋንጫ አስተናጋጇ ሩሲያ ልምድ ባላቸው አጥቂዎቿ አላን ድዛጎኤቭ ፊዮዶር ስሞሎቭ ታግዛ በቤቷ ጥሩ ደረጃ ለመያዝ ትጫወታለች ተብሎ ይጠበቃል።

ብራዚል

የዓለም ዋንጫው የአምስት ጊዜ አሸናፊዋ ብራዚል እንደ ኔይማር ጋብሬል ጀሱስ እና ፊሊፔ ኮቲንሆ ያሉ ተጫዋቾችን ይዛ በሞስኮ ትታደማለች።

ኢራን

ኢራን ወደ ዓለም ዋንጫ ስታልፍ የአሁኑ አምስተኛዋ ሲሆን፥ በሩሲያው የዓለም ዋንጫም የእስያ ዞንን ከወከሉ ሀገራት አንዷ ሆናለች።

ጃፓን

ጃፓን በዓለም ዋንጫው ለተከታታይ ስድስተኛ ጊዜ የሚያሳትፋትን ትኬት ቆርጣለች፤

ሜክሲኮ

ሜክሲኮ ከዚህ ቀደም በነበሩት የዓለም ዋንጫዎች የነበራትን ምርጥ ተፎካካሪነት አሁንም እንደምትደግመው ይጠበቃል።

ቤልጅየም

ዓለም በማግባትና ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል የመሰከረላቸው ኬቪን ደ ብሩይነ፣ ኤዲን ሃዛርድ እና ሮሜሉ ሉካኩ የመሳሰሉ ቁልፍ ተጫዋቾችን ይዛ ወደ ሞስኮ ታቀናለች።

ደቡብ ኮሪያ

ለዘጠንኛ ተከታታይ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ጨዋታ መሳተፏን ያረጋገጠችው የእስያ ዞን ተወካይ ደቡብ ኮሪያ የቶተንሃሙ ኮከብ ሰን ሄዩንግ ሚን እና ሌሎችም ተጫዋቾች ይዛ ለተቃራኒ ሃገራት ፈታኝ እንደምትሆን ይጠበቃል።

ሳዑዲ ዓረቢያ

ሳዑዲ ዓረቢያ ላለፉት ሁለት የዓለም ዋንጫዎች ሳታልፍ ብትቀርም አሁን ለአምስተኛ ጊዜ መሳተፏን አረጋግጣለች።

በቀድሞው የአርጀንቲና አሰልጣኝ ኤድጋርዶ ባውዛ የምትመራው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገር ሳዑዲ ሞስኮ እንደምትከትም አረጋግጣለች።

ጀርመን

ቶማስ ሙለር፣ ቶኒ ክሩስ፣ ቲሞ ዌርነርና ሌሎች ከዋክብትን የያዘችው አውሮፓዊት ሀገር፥ በተለያዩ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከ39 በላይ ግቦችን ማስቆጠሯ አሁንም የዓለም ዋንጫው ጠንካራ ቡድን ያደርጋታል።

እንግሊዝ

በጋሬዝ ሳውዝጌት የሚመሩት ሶስቱ አናብስት በማጣሪያ ጨዋታዎች ወደ ዓለም ዋንጫው ለመግባት ቀሏቸው ነበር።

ሆኖም የአጥቂ ክፍተት አሁንም የሚታይባት እንግሊዝ በቶተንሃሞቹ ሃሪ ኬን እና ዴሌ አሊ ከፊት ለመምራት አቅዳለች።

ስፔን

በወጣት ተጫዋቾቿ ወደ ሞስኮ የምታቀናው ስፔን በዓለም ዋንጫው ከፍተኛ የማሸነፍ ግምት ካላቸው ሀገራት አንዷ ሆናለች።

ናይጀሪያ

ምዕራብ አፍሪካዎቹ ንስሮች በአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታዎች የነበራቸው ያለመሸነፍ ጉዞ በሩሲያው የዓለም ዋንጫም ተጠባቂ አድርጓቸዋል።

በተለይም በምድብ ማጣሪያዎች ላይ በየጨዋታው በአማካይ ሁለት ግብ እያስቆጠሩ መምጣታቸው የማጥቃት አጨዋወታቸው ማሳያ ተደርጓል።

ቪክቶር ሞሰስ፣ ኬሌቺ ኢሃናቾ፣ አህመድ ሙሳ፣ አሌክስ ኢዮቢ እና ሌሎችም ተጫዋቾች የንስሮቹ ቁልፍ ተሰላፊዎች ናቸው።

ኮስታሪካ

በሩሲያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ከሚጠበቁ ተቀናቃኝ ሀገራት አንዷ ኮስታሪካ ናት።

ፖላንድ

የባየር ሙኒኩ አስፈሪ አጥቂ ሮበርት ሌዋንዶውስኪ ሀገር ፖላንድ፥ በሞስኮ የዓለም ዋንጨው ድምቀት ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል።

ግብፅ

ፈርኦኖቹ ከፈረንጆቹ 1990 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ሲሳተፉ የአሁኑ የመጀመሪያቸው ነው።

የሊቨርፑሉ ሞሃመድ ሳላህ አምስት ግቦች የግብጽን የሩሲያ ጉዞ የቀና አድርገውታል።

አይስላንድ

አይስላንድ ክሮሺያ፣ ቱርክ እና ዩክሬን በሚገኙበት ምድብ አሸንፋ ቀዳሚ በመሆን ነበር በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ ወደ ሩሲያ ማምራቷን ያረጋገጠችው።

ሰርቢያ
በ2012 እና 2016 የአውሮፓ ዋንጫ እንዲሁም በ2014 የዓለም ዋንጫ ያልተሳተፈችው ሰርቢያ አሁን ወደ ሞስኮ የሚወስዳትን ትኬት ቆርጣለች።

አሰልጣኝ ስላቮልጁብ ሙስሊን በማጣሪያ ጨዋታዎች ምክንያት እየተተቹ ሲሆን፥ የመባረር ስጋትም አለባቸው።

ሆኖም እሳቸውን የሚተካ ቋሚ አሰልጣኝ አለመገኘቱ ሌላው አጣብቂኝ ጉዳይ ነው፤ አሰልጣኝ ሙስሊን በተጫዋች አመራረጥ እና በታክቲክ አቀራረብም ቅሬታ ይቀርብባቸዋል።

ፈረንሳይ

ባለተሰጥኦ ወጣት ተጫዋቾችን የያዘ ስብስብ ስለመሆኑ ይነገርለታል።

ፖል ፖግባ፣ አንቷን ግሪዝማን፣ ኪሊያን ምባፔ፣ አንቶኒ ማርሻል፣ ኦስማን ደምበሌ፣ ንጎሎ ካንቴ እና ቶማስ ሌማር የስብስቡ አካል ናቸው።

ሆኖም በ2018 በሩሲያ በሚደረገው የዓለም ዋንጫ የፈረንሳይ አሰልጣኝ ዲዲየር ዴሻምፕ ብቁ ተፎካካሪና አሸናፊ ለመሆን የተጫዋቾችን የግል ብቃት ወደ ቡድን ማምጣት ይችላሉ ወይ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።

ፖርቹጋል

የ2016 የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊዋ ያለ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በዓለም ዋንጫው ማሸነፍ እንደምትችል በአውሮፓ ዋንጫው አሳይታለች ተብሏል።

ለዚህም ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከፈረንሳይ ጋር በነበረው የፍፃሜ ጨዋታ በጉዳት ባይኖርም ፖርቹጋል ግን አሸንፋ ዋንጫውን ማንሳቷ ማሳያ ሆኖ ቀርቧል።

ይሁን እንጂ በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች እና በአውፓ ሊጎች ድንቅ የማግባተ ችሎታ ያለውን የዓለም ኮከብ ተጫዋች ክርቲያኖ ሮናልዶን ሞስኮ ላይ ከፊት እንዲያጠቃ አሁንም መርጣዋለች።

ፓናማ፦ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ መሳተፋቸውን ካረጋገጡ ሀገራት አንዷ ሆናለች።

አርጀንቲና

የባርሴሎናው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ሀገሩን በመጨረሻ ሰዓት በኢኳዶር ላይ ባስቆጠራቸው ድንቅ ሶስት ግቦች ወደ ሞስኮ እንድታመራ አስችሏታል።

ከሜሲ ባሻገር አንሄል ዲማሪያ፣ ሰርጂዮ አጉዌሮ፣ ፓውሎ ዲያባላ፣ ጎንዛሎ ሄጊዌን የብሄራዊ ቡድኑ ስብስብ መሆናቸውም በ2018ቱ የዓለም ዋንጫ አስፈሪ ቡድን እንደሚሆን ግምት አግኝቷል።

ኮሎምቢያ

ደናሾቹ ንጉሶች በደቡብ አሜሪካ ዞን የማጣሪ ጨዋታዎች ከመውደቅ ተርፈው ወደ ሩሲያ እንደሚያቀኑ አረጋግጠዋል።

ኮሎምቢያ ሃሜስ ሮድሪጌዝ፣ ራዳሜል ፋልካኦ፣ ሁዋን ኳድራዶ፣ ዬሪ ሚና እና ዳቪንሰን ሳንቼዝን ይዛ ወደ ሞስኮ ታመራለች።

ኡራጓይ

በሉዊስ ሱዋሬዝ ልዩ ክስተቶች የምትታጀበው ኡራጓይ በ2018 የዓለም ዋንጫ መድረክ ትጠበቃለች።

ሴኔጋል

በሳዲዮ ማኔ ድንቅ ብቃት በሩሲያ ከሚደምቁት አፍሪካዊ ሀገራት አንዷ ናት ሴኔጋል።

ከደቡብ አፍሪካ ጋር በነበራት ጨዋታ ተሸንፋ የነበረችው ሴኔጋል፥ ጋናዊው ዳኛ ያልተገባ ውሳኔ ወስነዋል በሚል ተቀጥተው ጨዋታውም በድጋሚ ባለፈው ሳምንት ተደርጎ በማሸነፏ ወደ ዓለም ዋንጫው ማለፏን አረጋግጣለች።

ሞሮኮ

በ20 ዓመታት ውስጥ በዓለም ዋንጫ ስትሳተፍ የመጀመሪያዋ ሲሆን፥ በመጨረሻው የምድብ የማጣሪያ ጨዋታ አይቮሪ ኮስትን አሸንፋ ወደ ሩሲያ ማምራቷን አረጋግጣለች።

ቲኒዚያ

በዓለም ዋንጫ ስትሳተፍ የአሁኑ አምስተኛዋ ነው፤ የአሁኑ ብሄራዊ ቡድኗ ስብስብ በዋናነት ከሃገር ውስጥ ክለቦች የተውጣጣ ነው።

ስዊዘርላንድ

የማጣሪያ ጨዋታዎችን በብቃት አሸንፈው ወደ ዓለም ዋንጫ መግባታቸውን ካረጋገጡ ሀገራት አንዷ ስዊዘርላንድ ናት።

ዤርዳን ሻኪሪ፣ ብሬል ኤምቦሎ፣ ግራኒት ዣካ፣ ሪካርዶ ሮድሪጌዝ የብሔራዊ ቡድኑ ቁልፍ ተጨዋቾች ናቸው።

ፔሩ፦ ደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ወደ ዓለም ዋንጫ ዘግይተው ማለፋቸውን ካረጋገጡ ሀገራት አንዷ ናት።

ክሮሺያ

በአውሮፓ ምድብ የደርሶ መልስ ማጣሪያ ጨዋታ ግሪክን አሸንፋ ነው ወደ ሩሲያ ማምራቷን ያረጋገጠችው።

እንደ ሉካ ሞድሪች፣ ኢቫን ራኪቲች፣ ማሪዮ ማንዙኪች፣ ኢቫን ፔርሲች፣ እና ኒኮላ ካሊኒችን የመሳሰሉ ብቁ ተጫዋቾች ባለቤት የሆነችው ክሮሺያ፥ ለመውደቅ ጫፍ ላይ ብትደርስም በመጨረሻ ሰዓት ትኬቷን ቆርጣለች።

አውስትራሊያ

በአህጉራዊ የደርሶ መልስ ጨዋታ ሆንዱራስን በመርታት በመጨረሻዋ ሰዓት ወደ ሩሲያው የዓለም ዋንጫ ማለፏን አረጋግጣለች።

Comments

comments