የትግራይ ፖለቲካዊ ፖሊሲ፦ by ልፋዓተይ ተስፋ

==============

ትግራይ ፓሊሲን የሚያስፈፅም ኣመራር ሳይሆን ፤  የህዝቡ ተጨባጭ ችግር የሚፈታ ኣመራር ያስፈልጋታል። ትግራይ የህዝቡ ተጨባጭ ችግር የሚፈታ ኣመራር የምትሻ ከሆነ ደግሞ የተማሩና ተኣምር መስራት የሚችሉ ልጆቿን መጠቀም ግድ ይላታል ። ይህ ይሳካ ዘንድም የትግራይ ፖለቲካ በበጎ ዓይን ተመልክቶ መፍቀድና ሁኔታዎችን ማመቻቸት ኣለበት። እንደሚታወቀው ፖለቲካ የኣንዲት ሃገር ሁለንታዊ ሹፌር ነው ። ይህ ሾፌር ጤነኛ ፤ ብልህና ኣዋቂ ከሆነ መኪናዋን(ህዝቡን) ለረጂም ዓመታት የመምራት ዕድል ብቻ ሳይሆን ብቃትም ይኖረዋል።

 

የትግራይ ፖለቲካዊ ፖሊሲ በማይመለከታቸው ሰዎች ከላይ ወደታች (ከፌዴራል ወደ ቀበሌ) ተቀርፆ የወረደ ነገር ግን የህዝቡን ተጨባጭ ችግር የማይፈታ ፓሊሲን የሚያስፈፅሙ ኣመራር እንጂ ከታች (ከቀበሌ ወደ ፌዴራል) በህዝቡ ፍላጎትና ተሳትፎ የህዝቡ ዋና ችግር ማዕከል ያደረገ ነገር ግን በችግሩ ዙሪያ የሚመለከታቸውን ባለሞያዎች የሚመሩት ፖሊሲ ተግባራዊ ሆኖ ኣያውቅም ። የትግራይ ፖሊሲዎች ከላይ ወደ ታች እንጂ ከታች ወደ ላይ ኣይደሉም ። ይህ ደግሞ ትልቅ ስህተት ነው ።  “እናውቅልሃለን” የሚል ኣባዜ የተጠናወታቸውና ለዚህ ስልጣን ይቆናጠጡ ዘንድ በጭቁን የትግራይ ልጆች መስዋእትነት ለዚህ ወንበር ኣብቅተውት ሲያበቁ የሚያስስተዳድሩትን ጭቁን ህዝብ መልሶ መናቅ የሚያሳይ ፖሊሲ ነው። (ይህ ፅሁፍ የጤና ፖሊሲን ኣይመለከትም)

 

ኣንድ ፖሊሲ ኣውጪ የመንግስት ሚኒስቴር መ/ቤት ስለሚያወጣው ፖሊሲ የፈለገ ተኣምር ቢፈጠር የችግሩ ባለቤት ከሆነው ህዝብ የበለጠ ስለችግሩ ግንዛቤ ሊኖረው ኣይችልም። ምክንያቱም ያ ስለተቀረፀው ችግር ፈቺ ፖሊሲ የችግሩን ባለቤት የሆነው (ህዝቡን) ያላሳተፈ ፖሊሲ የህዝቡን ችግር የሚፈታ ፖሊሲ መቅረፅ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ብቻ ሳይሆን ሌላ ተጨማሪ ችግር ፈጣሪ ፖሊሲ  ከመሆን ኣያልፍም ። እንግዲያውስ የትግራይ ፖለቲካዊ ፖሊሲዎች በእንዲህ የታጨቁ መሰል ፖሊሲዎች ከሆኑ እነሆ 17 ዓመታት ሞላቸው ።

 

ከላይ የወረደ ፓሊሲን የሚያስፈፅም ኣመራር ሳይሆን የህዝቡ ችግርን ቀርፆና በልማታዊው ፖሊሲ ኣካትቶ ሰርቶ የሚያስሰራ ኣመራር ይበልጥ ልማታዊና ህዝባዊ ኣመራር መሆን ይቻላል። ከላይ የወረደ ፓሊሲ ትክክል ከሆነ  ፖሊሲው እስኪፈፀም ድረስ ኣመራሩና ህዝቡ ትክክል ይሰራል ፤ ያ ከላይ የወረደ ፓሊሲ ትክክል ካልሆነ ግን ፖሊሲውም ኣይፈፀምም ፤ ኣመራሩና ህዝቡም ትክክል በመስራት ጊዜውን ገንዘቡን እና ጉልበቱን ኣያባክንም። ስለዚህ ከላይ የሚወጡ ፖሊሲዎች ህብረተሰቡን ፤ መልክዓ ምድሩን እና ኣስፈፃሚውን ኣካል ግምት ውስጥ ያስገቡና የህብረተሰቡን ተጨባጭ ችግር ፈቺ መሆናቸውን ተገምግመው መውረድ ኣለባቸው።  ትግራይ ፖለቲካዊ ፖሊሲ ሳይሆን የትግራይ ህዝብ ችግር የሚፈታ ህዝብን እና የትግራይ ምሁራንን ያሳተፈ ህዝባዊ  ፖሊሲ ያስፈልጋታል። ህዝባዊ  ፖሊሲ በተራው የትግራይ ህዝብ እና በተጋሩ ምሁራን ተሳትፎ በየዘርፉ መስሪያ ቤቶች/ቢሮዎች የሚቀረፅ የትግራይ ህዝብን ሁለንተናዊ ችግሮችን ፈቺ ሆኖ ከታች ወደላይ (ከቀበሌ ወደ ፌዴራል) የሚዘረጋ ፖሊሲ መሆን ኣለበት።

 

ዛሬ ዛሬ ኣንዲት የትግራይ እናት “ልጆቼ የተሰውት’ኮ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥልኝ ነው” ስትል ፡ ሌላይቱ እናት ግን “ኢህኣዴግን የመረጥነው’ኮ ውሃ ፤ መብራት ፤ ኣስፋልትና ህንፃ እንዲሰራልን ብቻ ሳይሆን ከዚህም በላይ መስራት ስላለበት ነው” የምትል እናት ነው ያለቺው።

 

ኣስቡት እንግዲህ እነዚህ 2 ዓይነት እናቶች በኣንድ ሃገር እየኖሩ በኣንድ የፌዴራል መንግስት የሚተዳደሩ እናቶች ናቸው ። የትግራይ እናት የራሷና የልጆቿ ደምን ስለሌሎቹ እናቶችና ስከነተሳዳቢዎቹና ዲንጋይ ወርዋሪዎቹ ልጆቻቸው ከፍላ ኣሁንም ንፁህ ውሃ ያጣች እናት ናት ትግራወይቲ እናት😎 የመቐለ ውሃ ችግር በባህር ዳር ፡ ወይም በጎንደር ፤ ወይም በጂግጂጋ ኣልያም በኣዳማ ፤ ነቀምት ቢከሰት ኖሮ ኣይደለም የየክልሎቹ ርእሰ መስተዳድሮች ፡ የኢህኣዴግ ባለስልጣናት ጆሮ ዳባ ልበስ ይሉ ነበር ወይ? የሚለውን ህሊናዊ ጥያቄ ለናንተ ልተወው ፤ ምክንያቱም የኢህኣዴግ ባለስልጣናት እንኳን ደሙን ገብሮ ውሃን ላጣው ሆደ ሰፊው የመቐለ ህዝብ ለጅቡቲ ህዝብም በየቀኑ በብዙ ኩቢክ ሊትር የሚገመት ከ1000 ቦቴ ውሃ በላይ በየቀኑ እንዱሚያቀርብ ይታወቃል ።

 

ለመቐለ ህዝብ የውሃን ደህንነት ኣለማረጋገጥ ማለት ትግራይንና ተጋሩን ከሃገሪቱ ዓመታዊ በጀት ከሚመደብላቸው ሁለንታዊ መሰረተ ልማት ማግለል ማለት ነው ። ውሃ የለም ማለት ጤና የለም ማለት ነው። ውሃ የለም ማለት ግምባታ/construction የለም ማለት ነው። ውሃ የለም ማለት መንገድ የለም ማለት ነው። ውሃ የለም ማለት ህዝቡ በላቡ ያገኘውን ሳንቲም የታሸገን ውሃ/”Highland” or plastic water በመግዛት ስለሚያባክነው ኣይቆጥብም  ማለት ነው። ውሃ የለም ማለት ምግብ የለም ማለት ነው። ውሃ የለም ማለት ጎብኚዎች የሉም ማለት ነው። ውሃ ከሌለ የዚያን ማህበረሰብ ገፅታ  ክፉኛ እንደሚያበላሸው ግልፅ ነው ። ውሃ ለሰው ልጅ ቀርቶ ህይወት ላላቸው ነገሮች ከምግብ ፤ ፆታዊ ግንኙነት(ልጅን ለመተካት) ፤ ከኣየር የሆኑት መሰረታዊ ነገሮች የሚመደብ ወሳኝ/Physiologic need ነው። ለሰው ልጆች ንፁህ ውሃን ማቅረብ እስከ ፕላን የሚባል ነገር የሚቆይ ጉዳይ ኣይደለም።

 

በተጨባጭ  ነገር ብናየው እውነት መቐለ ውሃ ጠፍቶ እንዳልሆነ ግልፅ ነው ። እንዲያውም በመቐለ የተትረፈረፈ ውሃ ነው ያለው። የቀላሚኖ ፤ የዒላላእና የገረብ ፀዶ ውሃ ጠገብ ቦታዎችን ጨምሮ በከተማዋ ባሉ በርካታ ድልድዮች የተሰሩባቸው ትልልቅ ወንዞች በከንቱ የሚፈሰው ውሃ ከትርፍም በላይ ነው ። ይህ ውሃ በጥቂት የውሃና የጨው ህክምና/Salt Water Therapy ለህዝቡ ና ለከተማዋ መሰረታዊ ኣገልግሎት በቀላሉ ማዋል ይቻላል። ይህ ቀላል ነገር ፡ ነገርግን መሰረታዊ ነገር ተግባራዊ ለማድረግ የትግራይ ፖለቲካዊ ፖሊሲ ትንሽ በጀት ከቅንነት ብቻ ይጠይቃል ።

 

ይህ ኣማራጭ እንኳ መጠቀም ባይቻል ፤ ከውቅሮ 2 ኣውላዕሎ እስከመቐለ ያለው ርቀት ያን ያክል ኣይደለም ። የኢህኣዴግ መንግስት ገንዘብ ለማትረፍ ከኣርባ ምንጭ የኣባያ ሃይቅ እስከ ጅቡቲ የተፈጥሮ ጋዝን የሚያስተላልፍ ቱቦ መዘርጋት ከቻለ ደሙን ኣፍስሶ የመጠጥ ውሃን ላጣው የትግራይ ህዝብ ህይወት ለማትረፍ ከውቅሮ 2 ኣውላዕሎ እስከመቐለ የንፁህ ውሃ ማስተላለፊ ቱቦ ለመዘርጋት እንዴት ያቅተዋል??? የመቐለ ህዝብ’ኮ ከጅቡቲኣውያን ይልቅ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ናቸው!!!

 

የትግራይ ፖለቲካዊ ፖሊሲ በጣም የሚያሳዝንና በየደረጃው ባሉ ምክርቤቶች ተኣማኒነት የሌላቸው ሪፖርቶችን በማቅረብ የተጠመደ ስንኩል ፖሊሲዎች እንዳሉ ይታወቃል ። የትግራይ የትምህርት ፖሊሲን ብንመለከት እንኳ፦

 

ከ4፤5 ዓመታት በፊት ከሃገሪቱ የመሰናድኦና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ተፈታኞች (Grade 10 & 12 Matriculation & Entrance ,respectively)መካከል በከፍተኛ ነጥብ ያስገቡ የነበሩት የትግራይ ትምህርት ቤቶች ናቸው ። ይህም የሆነበት ምክንያት በርካታ ቢሆንም ዋና ዋናዎቹ ግን፦

 

=> በየ ት/ቤቱ ለሞያው ክብርና ፍቅር የነበራቸው/ያላቸው ብቁና ተወዳዳሪ መምህራን ይቀጠሩ ስለነበር ፤

 

=> መምህራኑ ከድርጅታዊ ፖለቲካ ጫና ነፃ ስለነበሩ ፤ ወይም የመምህራኑ የፖለቲካ ኣመለካከት ከት/ቤቱ ውስጥ ያንፀባርቁ ስለነበር ፤

 

=> መምህራኑን የማብቃት ፤  የመማሪያ ግብአትን ማቅረብና ተፈላጊውን ባለሙያ ለየዘርፎቹ የማፍራት ስራ ይሰራ ስለነበር ፤

 

=> ለመምህራኑ ኣስፈላጊውን ክብር ይሰጥ ስለነበር ፤

 

=> ለትምህርት ጥራት በመምህራን ፤ በተማሪዎችና በተማሪ ወላጆቹ ሶስቲዮሽ ግንኙነት ክትትልና ቁጥጥር ይሰራ ስለነበር ፤

 

=> ተማሪዎቹ ከየት/ቤታቸው ካለ ኣድልዎ በውጤታቸው ተመልምለው ቀላሚኖ እና MIT ይገቡ ስለነበር ፤

 

=> የቀላሚኖ መምህራን ቅጥር ነፃ ፤ ግልፅና በውድድር የሚፈፀም ስለነበር ፤

 

እነዚህ ጥቂቶቹ ነበሩ ።

 

በዚህ ግዜ ማለትም ከ4፤5 ዓመታት በፊት ከሃገሪቱ የመሰናድኦና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ተፈታኞች (Grade 10 & 12 Matriculation & Entrance ,respectively) መካከል በከፍተኛ ነጥብ ያስገቡ የነበሩት የትግራይ ትምህርት ቤቶች ነበሩ ።

 

ዘንድሮስ ???  ለምን ???

 

በሃገሪቱ ቀርቶ ምናልባትም በዓለም ለመምህራን ከፍተኞውን ክብር የሚሰጥ ህዝብኮ የትግራይ ህዝብ ነው። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ መምህራንን ጎንበስ ብሎ እጅን በመንሳት “መምህረይ” ብሎ የሚጠራ ህዝብ ነው ። እናም የክልሉ ት/ት ቢሮ ለመምህራን ተገቢውን ክብር ከነ ጥቅማ ጥቅሞቸ ይስጥ ኣይስጥ ሌላ ጉዳይ ሆኖ የትግራይ ህዝብ ግን መምህራንን ከልብ ያከብራል ። ታድያ ዘንድሮስ ልጆቹ ልክ እንደ የዛሬ 4 እኔ 5 ዓመታት በፊት ከሃገሪቱ የመሰናድኦና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ተፈታኞች ከፍተኛውን ነጥብ ማምጣት ለምን ኣቃታቸው???  ለምን ???

 

በትግራይ የት/ት ጥራት ኣልተረጋገጠም ። በኣሁን ሰዓት ያለው የትግራይ ከስርዓተ ት/ቱ (Curriculum) ጀምሮ እስከ ሪፖርቱ ያልተጠና እና በስህተት የተሞላ ነው። የትግራይ ስርዓተ ት/ቱ (Curriculum) የህዝቡና የክልሉ ታሪካዊ ፤ ባህላዊ/ሃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ተጨባጭ ሁኔታን የማይገልፅ ፤ የማያስተምር ፤ በኣማራ ልሂቃን የተቃኘ(ከኣማራነት ወደ ጥንታዊውና ትክክለኛ ማንነቱ ያልተመለሰ) እና የማያመራምር ነው። የትግራይ ስርዓተ ት/ት በማይመለከታቸው ሰዎች የተቀረፀ ለትግራይና ተጋሩ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የሚመች ተደርጎ የተቀረፀ ጎዶሎና ስህተት የሆነ ስርዓተ ትምህርት ነው ያለው ።

 

ለምሳሌ የትግራይና ተጋሩ ታሪካዊ ፤ ባህላዊ/ሃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ዳራዎች 100% የተፃፉት በግእዝ ቋንቋ ነው። በትግርኛ ቋንቋ የተፃፈው የህወሓት ፖለቲካዊና ታሪካዊ ዳራዎች ብቻ ነው።  የህወሓት ፖለቲካዊና ታሪካዊ ዳራዎች ደግሞ ከትግራይና ተጋሩ ጠቅላላ ታሪካዊ ፤ ባህላዊ/ሃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ዳራዎች የ17 ዓመታት ለ3500 ዓመታት(የተጋሩ ማንነት በግእዝ ቋንቋ የተፃፈበት ዘመናት) መቶኛ/Ratio/ ብቻ ማለትም  ከ 0.0071 ያነሰ ድርሻ ነው ያለው። ይህም ማለት የተጋሩን ማንነት ከመግለፅ ኣኳያ ትግርኛ ቋንቋን ከግእዝ ቋንቋ ጋር ስናነፃፅረው ኢምንት ነው። ስለሆነም የግእዝን ቋንቋ በስርዓተ ት/ቱ ያላካተተ የትግራይ ስርዓተ ት/ት በጣም ኣሳፋሪና እጅግም ስሕተት ነው። የትግራይ ስርዓተ ት/ት በሳምንት 3 ክፍለ ግዜ ለኣማርኛ ሲሰጥ “ኣማርኛ የተጋሩ ታሪካዊ ፤ ባህላዊ/ሃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ዳራዎች ይገልፃል ወይ? ካሁን በፊትስ ይህ ቋንቋ ስለተጋሩ ሁለንተናዊ ማንነት በመፅሃፍ ፤ በትያትር ፤ በፊልም ፤ በተውኔት ይግልፅ ነበር ወይ?” የሚለውን መጠይቅ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።

 

የትግራይ ማንነት በቅዱስ ያሬድ ስራዎች ውስጥ የምናይ ከሆነ ይህ የሆነው በግእዝ ቋንቋ እንጂ በኣማርኛ ቋንቋ የተፃፈ ኣይደለም ፤ ስለሆነም ተጋሩ የግእዝን ቋንቋ መማር ማንነታዊ ግዴታቸው ነው።

 

የትግራይ ማንነት በጥንታውያን ኣኽሱማውያን ነገስታት ውስጥ የምናይ ከሆነ ይህ የሆነው በግእዝ ቋንቋ እንጂ በኣማርኛ ቋንቋ የተፃፈ ኣይደለም ፤ ስለሆነም ተጋሩ የግእዝን ቋንቋ መማር ማንነታዊ ግዴታቸው ነው።

 

የትግራይ ማንነት በጥንታውያን የብራና መፃህፍት በሆኑት በዓውደነገስታት ፤ በክብረ ነገስታት ፤ በፍትሃ ነገስታት ውስጥ የምናይ ከሆነ ይህ የሆነው በግእዝ ቋንቋ እንጂ በኣማርኛ ቋንቋ የተፃፈ ኣይደለም ፤ ስለሆነም ተጋሩ የግእዝን ቋንቋ መማር ማንነታዊ ግዴታቸው ነው።

 

የትግራይ ማንነት በጥንታውያን የተጋሩ የጥበብና የኪነ ህንፃዎች ስራዎች ውስጥ የምናይ ከሆነ ይህ የሆነው በግእዝ ቋንቋ እንጂ በኣማርኛ ቋንቋ የተፃፈ ኣይደለም ፤ ስለሆነም ተጋሩ የግእዝን ቋንቋ መማር ማንነታዊ ግዴታቸው ነው።

 

የተጋሩ ኣብዛኛው ሃይማኖታዊው ቅርስና ኣገልግሎት(ቅዳሴን ጨምሮ) በግእዝ ቋንቋ እንጂ በኣማርኛ ቋንቋ የተፃፈው ኣይደለም ፤ ስለሆነም ተጋሩ የግእዝን ቋንቋ መማር ማንነታዊ ግዴታቸው ነው።

 

የተጋሩ መንደሮች ፤ የመጠርያ ስሞች ፤ የዓውደ ውጊያ ታሪኮች የምናይ ከሆነ ይህ የሆነው በግእዝ ቋንቋ እንጂ በኣማርኛ ቋንቋ የተፃፈ ኣይደለም ፤ ስለሆነም ተጋሩ የግእዝን ቋንቋ መማር ማንነታዊ ግዴታቸው ነው።

 

በኣጭሩ የግእዝ ቋንቋ ኣለመማር ማለት የትግራይና ተጋሩ ማንነት ማጣት ማለት ነው። ማንነት የሌለው ህዝብ ደግሞ ክብር ኣይኖረውም ፤ የሰራውን ስራ ፤ ያካበተውን ቅርስ ማንም ኋላ ቀር ህዝብ/ኣካል/ማህበር ሲዘርፈው ቆሞ ከመመልከት ውጪ ሌላ ኣማራጭ ኣይኖረውም ። ምክንያቱም እኔ እየተዘረፈ ያለውን ንብረት የኔ መሆኑን ካላወቅኩኝ የኔ ነው ብየ ንብረቱን ከመዘረፍ የማዳን ሃላፊነትም ፤ እውቀትም ሞራልም ኣይኖረኝም ። የታሪካችን የኛነት ሃላፊነት ፤ እውቀት እና ሞራል የምናገኘው ሁሉም ነገራችን በተፃፈው የግእዝ ቋንቋን ስንማር ብቻ ነው።

 

የትግራይ የትምህርት ጥራት በይዘቱ ብቻ ሳይሆን በሪፖርት ደረጃም የሞተ ነው። ለምሳሌ በዓመቱ መጀመሪያ በኣንድ ክፍል 60 ተማሪዎች መዝግቦ ቢያስተምር እና በት/ት ዓመቱ መሃከል 3 ተማሪዎች በሞት ፤ ወይም በህመም ፤ ወይም በተለያየ ኣጋጣሚ ከት/ት ገበታቸው ቢገለሉ በት/ት ዓመቱ መጨረሻ 60 ተማሪዎች ኣስተምሬኣለሁ ብሎ ሪፖርት እንደሚያደርግ እርግጠኛ ነኝ። የትግራይ ፖለቲካዊ ፖሊሲ ችግር ፈቺ ፖሊሲ ሆኖ ኣያውቅም።

 

ስለዚህ ትግራይ ፖለቲካዊ ፖሊሲ ሳይሆን የትግራይ ህዝብ ችግር የሚፈታ ህዝባዊ  ፖሊሲ ያስፈልጋታል።

 

<><><><><><><><><>///<><><><><><><><><>

 

በቀጣይ ክፍል የትግራይ ግብርናን እናያለን ፦

Comments

comments