የምትለወጥ እንጂ የምትፈርስ ሃገር አይደለችም by Fistum Berhane

* * * * * * * * * * * * * * * * * * * * * * * * * *

ለፅሁፉ መርዘም ይቅርታ እጠይቃለሁ

××××××××××××××××××××

 

“የቤት ልጅ” ነበርኩ..በያኔ አጠራር። በግዜ የምገባ መደባደብ የማልችል ቀዮ ነገር።

 

ታዲያ እንደዛ ሰትሆን ከሙሉ ቀን ትምህርት መልስ ሰፈር ሜዳ ላይ ኳስ መጫወት ፈተና ነው። በጊዜው ቋንቋ “ዱርዬ” የሰፈር ልጆች ያልፈቀዱለት ዳር ሆኖ ከማየት ውጪ አማራጭ የለውም። አንዳንዴ ከቤት የሚወዷትን አምባሻ ይዤ እወጣና ለጉልቤው ኤፍሬም አስረክቤ እጫወታለሁ።

 

አብዛኛውን ግዜ ግን ጓደኛዬና እኔ ዳር ላይ ቁጭ ብለን በዚህ ኢፍትሃዊነት እንበሳጭ ነበር።

ከተወሰነ ግዜ በኋላ ጓደኛዬ የሰፈራችን ጋራዥ ውስጥ ማገዝ ጀመረና በትልልቆቹ “ዱርዬዎች” እንደ “ትልቅ” ተቀባይነት አገኘ። ኳስ መጫወትም የሚከለክለው አልነበረም።

 

እኔና ሌሎቹ በጓደኛችን ከፍታ (እድገት ልበለው?) የተሰማን ደስታ ነበር። የኛ የጭቁኖቹ ሰው ትልልቆቹ ማህበር ገብቷላ! ከአሁን በኋላ ማን ይነካናል።

 

ደስታችን ብዙ አልቆየም። አሁን እኛ ላይ የሚበረታው “ትልቅ” ማን ቢሆን ጥሩ ነው? የትናንቱ ጭቁን ጓደኛችን።

 

ያ ግዜ ስለ መደብ ሽግግር የመጀመሪያ ክላስ የወሰድኩበት ነበር። ኋላ ላይ ሳነብ አዲስ አልሆነብኝም።

 

እና ምን ለማለት አካባቢ ነው….

 

የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንኳን ድሮ በኔ እድሜ እንኳ የአማራ እና ትግራዋይ ጨዋታ ተደርጎ ነበር የሚታየው። ሌላው እንደ አጫዋች።

 

ከሁለተኛዉ አብዮት (83) በኋላ እንኳ ሶስተኛው ተጫዋች (ኦሮሞ) በለወጡ  ደረጃውን አሻሽሎ የኢህአዴግ (የሶስት ብሄሮች ክለብ) አባል ሆኖ ከድሮው የተሻለ በጨዋታው ቢንቀሳቀስም በሁለቱ ተጫዋቾች እንደ ዋና ተጫዋች ሳይቆጠር እንደ እኔና ጓደኛዬ ዳር ተመልካች ሆነ። መጫወት ሲፈልግና እንቅስቃሴ ሲያደርግ “ተገንጣይ” በሚል ስጋት ተደርጎ ይሳልና እንዲሸማቀቅ ይሆናል።

 

ሌሎቹን 83ቱንማ ለፖለቲካ ጨዋታው የጠራቸውም አልነበረም።

 

ጉልበትና ፖለቲካ እያደር ይዳብራልና ከ97 በኋላ ብሎም ባለፉት 5 አመታት  በተለይ ደግሞ ካለፈው አመት ጀምሮ ኦሮሞ የሃገሪቱን የፖለቲካ ጨዋታ ከሁለት ፈረስ ሩጫ ወደ ሶስት ፈረስ ሩጫ (three horse race) ቀይሮታል። ነባር ተጫዋቾቹም ሌላ ተጫዋች መግባቱን ተቀብለውታል። ብዝሃነት ማለት ይሄ ነው።

 

በእርግጥ አሁንም ፊንፊኔን ላይ ያለውን ጥያቄ “ከመገንጠል በፊት መሬቱን የመያዝ” አድርገው የሚከሱ ስጋት ያልለቀቃቸው “ሃገር ጠባቂ” ነን ባዮች አሉ።

*

*

ከመለስ ሞት በኋላ የማእከላዊውን መንግስት መዳከም ተከትሎ ክልላዊ መንግስታት ለመንቀሳቀስ የተፈጠረላቸው ክፍተት ታድያ ተጨማሪ ተጫዋቾች ወደሜዳ ለመግባት አደፋፍሯል።

 

ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ የውስጥ መረጋጋትን ከፈጠረ በኋላ በኢህአዴግ እንዲሁም በፌዴሬሽኑ ተገቢ ቦታ ለማግኘት መንቀሳቀስ የጀመረው ሶማሊ ነው።

 

ኢህአዴግ በሚባለው የሶስት ብሄር አራት ክልል ክለብ የተያዘው ሜዳ ግን አሁንም ሌላ ተጫዋች ለመቀበል ከብዶታል።

 

እንደውም ከፊንፊኔ በብእር ስም በሚለቀቁ ፅሁፎችና በወዳጆቻችን ፌስቡከሮች እንዲሁም በሚኔሶታ አክቲቪስቶች “ሶማሊ ተገንጣይ”  የምትል ክስ ተሰምቷል። የወሰን ግጭቱም “ከመገንጠል በፊት መሬቱን የመያዝ” ዝግጅት አድርገው የሚከሱ ስጋቶች ታይተዋል።

 

ያው ልክ ጨዋታው ውስጥ ሲገባ እንደተቀየረብን የልጅነት ጓደኛችን ማለት ነው።

 

ዴዣቩ ሆነና የመገንጠል ተጠራጣሪዎች ኤርትራውያን ተጋሩ ኦሮሞ እያለ ሶማሊ ጋር ደርሷል።

 

ፖለቲካችን መስፋቱ አይቀርምና ቀጥሎ የሚመጣው አዲስ ተጫዋች አፋር  እንደሚሆን መገመት አይከብድም።

ያኔ እሱም በተገንጣይነት የመከሰስ ተራ ይደርሰዋል። በተለመደው ኡደት ከቀጠልን ደግሞ ከሳሹ ወደ ሜዳ የሚገባው አዲሱ ተጫዋች ይሆናል።

 

ማጠቃለያ

********

የዛሬ ሁለት ሳምንት ወዳጄ አባቡ ረሺድ በኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች መካከል ያለውን ፍትጊያ ታዝቦ “ቀጥሎ የምንሰማው ዜና መጀመሪያ የኢህአዴግን መፍረስ ሲቀጥል የሃገሪቱን መፍረስ ይሆናል” ሲል ስጋቱን ገልፆ ነበር።

ይሄ የአባቡ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች ነው። መንግስትም ማስፈራሪያ አድርጎ ስለሚጠቀምባት ይደጋግማታል። ልክ ባለፈው ሳምንት ጠቅላዩ “የሃገሪቱን ሰላም ኮምፕሮማይዝ አናደርግም” እንዳሉን ማለት ነው።

 

አባቡ ኢትዮጲያ አትፈርስም።

 

ኢህአዴግ ሊፈርስ ይችላል። በተለይ የጥቂት ፓርቲዎች ካርቴል እንደሆነ መቀጠል ከፈለገ አይቀርለትም። ስራው ያውጣው።

ኢትዮጲያ ግን መለወጧን ትቀጥላለች እንጂ አትፈርስም።

 

ወደ ኋላ ላይ ችላ ቢባልም በህገመንግስቱ አርቃቂዎች እንደታለመው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሜዳ እየሰፋና የሚገቡት ተጫዋቾች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ አይቀርም። የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች እየጎለመሱ…የተለያዩ ህዝቦችና ክልሎች ጨዋታው ውስጥ ተመልካቾች ሳይሆን ተሳታፊዎች ለመሆን መንቀሳቀሳቸው አይቀሬ ነው።

 

ይሄ ሂደት ሃገር አያፈርስም። ለጨዋታው አመቺ የሆነ ህገመንግስትም አለ።

 

እንደ አሁኑ ችግር የሚፈጠረው አዲስ ተጫዋችን የምናስተናግድበት አግባብ ካልተሻሻለ ነው።

 

(ሃገሪቱን ከብዝሃነት ፖለቲካ ወደ ኋላ ለመመለስ የሚደረግ ሙከራ የመፍረስ አደጋ ያመጣል ሊባል ይችል ይሆናል። እንደኔ እምነት ያ ሊሆን የሚችልበትን እድል እንደ ሃገር የተሻገርነው (ሃገራችን የተቀየረች) ሲሆን በዚያ መንፈስ የሚንቀሳቀስ ሃይል እራሱን ከማድከም ባለፈ ስኬታማ አይሆንም በሚል በዚህ ፅሁፍ ዘልየዋለሁ)

 

ስጋትና መንገድ መዝጋት ባህል ካደረግነው አዳዲስ ተጫዋቾች ደረጃቸውን ለማሳደግ የሚያደርጉት ሙከራ ቀውስ ውስጥ ሊከተን ይችላል።

የፖለቲካ ጨዋታችንን የሰለጠነና ህዝብ ጋር የማይወርድ አድርገን ካሻሻልነው ግን dynamic የሆነችና ሞቅ ያለ ፖለቲካ ያላት ሃገር ወደ መሆን እንሄዳለን እንጂ መፍረስ አያሰጋንም።

 

ባለፈው አመት የኦሮሞ ፕሮቴስት ላይ በፃፍኩት አርቲክል ላይ “ይሄ አመፅ ኢትዮጲያን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር ይሆናል” ያልኩበት ምክንያትም ከላይ የፃፍኩትን ሃሳብ ተመስርቼ ነው።

የሶማሊ ክልልን ድምፅን የማሰማት እድገት የማየውም በስጋት አይን ሳይሆን የዚሁ የኢትዮጲያ evolution ሂደት አካል አድርጌ ነው።

 

ወደ ጨዋታው ለመግባት የሚደረገው ጥረት ላይ ማድረግ የሚቻሉና የማይቻሉ ነገሮችን (ground rules) ማስቀመጥ/መስማማት ከቻልን ፖለቲካው የሃገሪቱን ሰላምም አንድነትም የማያሰጋ የኤሊት ድርድር ማድረግ እንችላለን። ፖለቲካ መሆንም ያለበት እንደዛ ነውና።

#TheFetsum

Comments

comments