ወዴት ወዴት ነው? የተጻፈን ትቶ ያልተጻፈን ማንበብ ምን አመጣው?  by ዘፀኣት ሴቭ ዓድና( Dr.)

 

እየተባለ ያለው እኮ ይህ ነው፥

ብዙሐኑ የትግራይ ወጣት ምሁራን ከዚህ ያልጠራ፣ በብዙ የተምታቱ የሚመስሉ ሐሳቦች የታጨቀ፤ የሚጠቅሙም የማይጠቅሙም አጀንዳዎች የተቀላቀሉበት እንቅስቃሴ ሶስት ጠቃሚ ነገሮችን ብቻ ይጠብቃል፤ የዝምታውና የከፊል ድጋፉ መሰረትም 3ቱ ናቸው፤

 

1- እንቅስቃሴው ልክ በልቡ ዝሆንን ስለማከል እንደሚያስብ እንቁራሪት እራሱን እጅግ አግዝፎ የሚመለከተውና በትምክሕት የተወጠረው የኤርትራ የከበሳ ፖለቲካል ኤሊት ባዶ ትምክሕቱና ትዕቢቱ በረድ ብሎለት ወደ ውስጡ እንዲመለከትና ነባራዊውን ሐቅ እንዲገነዘብ፤ በኤርትራ (በተለይም የከበሳው) ሕዝብ ላይ ያንዣበበው አደጋ አስተውሎ ሕዝቡን ከጥፋት እንዲያድን፤ በዚያ አካባቢ ሊነሳ የሚችል አደገኛ እሳት ለማስቀረት ጥረት እንዲያደርግ የማንቂያ ደወል ይሆንለታል የሚል ተስፋ አለ፤

 

2- እንቅስቃሴው የኤርትራ ሕዝብ በአጠቃላይ፤ በኤርትራ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የበላይነቱ በያዘው የከበሳ ሕዝብ ደግሞ በተለየ፣ የሸዐብያ ስርዐት በሕልውናው ላይ የደቀነው አደጋ እንዲገነዘብ ሊያደርግ፤ ለችግሮች ውጫዊ ጠላት የመፈለግና ወደ ውስጥ ለመመልከት ያለመፈለግ ሸዐብያ-ወለድ ባሕል እንዲቀረፍ፤ የኤርትራ ሕዝብ ለእልቂቱ፣ ለውድመቱ ቀንደኛ ተጠያቂው አጠገቡ ያለው ስርዐት እንደሆነ እንዲረዳ፤ በውጤቱም ሕዝቡ ስርዐቱን አንቅሮ እንዲተፋ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በምድሪ ባሕሪ የቤተ-አግአዚያን እንቅስቃሴ የሸዐብያን ስርዐት መሰረቱ ከሆነው የከበሳ ሕዝብ ሊያቆራረጠውና ከመሰረቱ ገዝግዞ የመጣል ዐቅም ያለው ነው፤ ይህ መቸም ለሑሉም ሕዝቦች ትልቅ ጥቅም ያለው ነው፤

3- እንቅስቃሴው ጀብሃና ሸዐብያ ከ50 ዐመታት በላይ፤ ጣልያን ከ50 ዐመታት በላይ ለሚልቁ ዐመታት በኤርትራ ሕዝብ ላይ በረጩት ትግራይ ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ መርዝ እንዲያመክን፤ በትግራይ ወጣቶች ዘንድ በተለይም ባለፉት ሁለት ዐስርት ዐመታት እያደገ የመጣው የንቀት አመለካከት እንዲያክም፤ በውጤቱም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲያጠናክር ተስፋ አለ፡፡ በተለይም በቋንቋ፣ በባሕል፣ በማንነት እጅግ የተዛመዱ የከበሳው ኤርትራ ሕዝብና አጠገቡ ያለው የትግራይ ህዝብ መካከል መልካም መቀራረብ እንዲፈጥርና በሁለቱ ሕዝቦች ያለው ድንበር ትርጉም ወደ ሌለው ደረጃ እንዲወርድ ሁኔታዎች እንዲያመቻች ይታሰባል፡፡

…….

ይህ ኢትዮጵያ የምታራምደውን ፌደራላዊ ስርዐትና “አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማሕበረሰብ ለመገንባት” የሚደረግ ጥረት ያግዛል እንጂ ሌላ አፍራሽ ተልዕኮ ሊኖረው አይችልም፣ ከሕገ-መንግስቱ ጋርም ምንም የሚጻረር ይዘት የለውም፣ የሀገራችን ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሞችንም የሚያስከብር ነው።

 

ሆኖም እንቅስቃሴው ሁሉንም አሳታፊና አቃፊ እየሆነ፤ ስሕተቶቹን እያረመ፣ እየጠራ፣ እየጠነከረ እንደሚሄድ፤ የታሪክ እባጮችንና ህፀፆችን አክሞና አርሞ፤ የወቅቱን ተግዳሮቶች አሸንፎ፤ ሰላምንና ፍቅርን ለተጠሙ ሕዝቦች እጅግ መልካም የሆነ ውጤት እንዲያጎናፅፍ ለሁሉም ጠቃሚ እንዲሆን በጥበብና በትዕግስት መገራት ይፈልጋል፡፡ እስካሁን ያ አልተፈጠረም፤ መፈጠር ግን አለበት፡፡

 

ኢትዮጵያ ከአክሱም ማሕፀን የተወለደች ሽል ናት፡፡ ኢትዮጵያዊነት የአባቶቼ ርስት፣ የአባቶቼ የዘመናት የመስዋዕትነትና የመባዘን ውጤት፣ የአባቶቼ ፕሮጀክት እንጂ ከማንም የተቀበልኩት፣ ለማንምም የምተወው አይደለም፡፡

Comments

comments