ራስን ማጥፋት ሀራም ስለሆነ ሳይሆን፣ ነገ አዲስ ቀን ስለሚሆን ኑር!!!!!!

በአንድ ወቅት በአሜሪካ ውስጥ አንድ ወጣት ልጅ ትምህርት ቤት ላሉ ጓደኞቹ ራሴን ላጠፋ ነው ይላቸዋል፣ ጓደኞቹም ይስቁበታል።

ከትምህርት ቤት መልስም አብረውት ላሉ ሰዎች ዛሬ የህይወቴ የመጨረሻ ቀን ነው፣ ራሴን ላጠፋ ነው ይላቸዋል፣ ሰዎች የእውነት አልመሰላቸውም ግን ቢሆንም አብሽር ለምን እንደዚህ ታስባለህ አንተ ልጅ ነህ ገና ብዙ መስራት ትችላለህ ይሉታል…. ልጁም ሰምቶ ሳይዋጥለት ወደቤቱ ይሄዳል።

ቤት ከገባ በዃላ የቤተሰቡ ስልክ ላይ ይደውላል፣ እናትና አባት ቤት ውስጥ የሉም። ደጋግሞ ይደውላል ስልካቸው አይነሳም፣ በመጨረሻም የህይወት ቅርብ ጓደኛው ጋር ይደውላል፣ ራሴን ላጠፋ ነው ቻው ይለዋል፣ ጓደኛው የምሩን እንደሆነ ስለገባው አምርሮ ይለምነዋል፣ ወዲያውም ወደ እናት ደጋግሞ ይደውልና ጓደኛው ራሴን ላጠፋ ነው እያለ እንደሆነ ይነግራታል። እናትም ትረበሻለች፣ ብትደውል ስልክ አይነሳም፣ ቤተሰብ ፍፁም ረብሻ ውስጥ ይገባሉ።

ወደጎረቤትም ይደውላሉ እባክሽን ሂጂና ልጄን እይው ራሱን ሊያጠፋ እንደሆነ እየዛተ ነው ትላታለች። ሴትዮዋም እንደተባለችው ትሄዳለች ብትጣራ ብትጮህ የሚከፍትላት የለም።

…… እንወድሀለን፣ እባክህን መጥፎ ነገር አትፈፅም….. ብትልም የሚሰማት ታጣለች። ልጁ እንደዛተው አድርጎታል።
ቤተሰብ ፍፁም ተረበሽ፣ ነገር ግን ሰአቱ ረፍዷል፣ ብቸኝነት፣ ጭንቀት የረበሸው ልጅ በሞት እገላገላለሁ ብሎ እስትንፋሱን ቆረጠ።

***

ይህ አማኝ ያልሆነ ሰው መሞት እንደ መገላገል ይመስለዋል። አማኝ የሆነ ሰው ግን ከሞት በዃላ ህይዎት እንዳለ የሚያምን ሙስሊም ግን በቀላሉ አይፈፅምም። ምን ይዤ ሲልም ይጨነቃል።

ብዙዎች ተስፋ ቆርጠዋል፣ ለመሞት ደግሞ ድፍረት የለም፣ ምክንያቱም ሀራም ነው። መረዳት ያለብን ግን በዚህ ስሜት ውስጥ መኖር አሁንም ከባዶነት ስሜት አያላቅቀንም። ተስፋ የሰው ልጅ ብቸኛው የመኖር ምክንያት ነው። ተስፋ አድርግ ነገ ከዛሬ የተሻለ ይሆናል በል። ትናንት የዛሬው ስሜትህ ይፈጠራል ብለህ እንዳልገመትክ ሁሉ ነገም የዛሬው ጉዳይ ያልፋል ብለህ ተስፋ አድርግ።

ከሁሉ በላይ ወደምድር የመጣህበትን አላማ ፈልገህ ማሳካት እንዳለብህ ተረዳና ኑር፣ አላህ ወደዚህ አለም እንደቀላል አላመጣህም፣ አንተም እንደቀላል ለመሄድ አታስብ፣ ስለዚህም ከሱ ጋር በፍቅር ተሳሰር፣ ጌታህን ውደደው ታዘዘው፣የብቸኝነት ስሜት፣ የተስፋ መቁረጥ ስሜት፣ ማንም የለኝም፣ ማንም አይወደኝም ወደሚል ስሜት ያመጣህ ከአምላክህ ጋር ያለህ ግንኙነት መበላሸቱ ነውና ተመለስ፣ እርሱን አስደስት እሱ ደግሞ አንተን ያስደስትሀል።

ተፀፅቻለሁ፣ የሰራሁት በደልና ጥፋት ከመንገድህ አስወጥቶ እያስጨነቀኝ ነውና ጌታየ ሆይ እረፍትን ስጠኝ በለው።
ሀዘን ስለሚያደክምህ ሳይሆን ደስታ የሚሰጠው ብዙ ነገር ስላለው ብቻ ተደሰት!!!!!

አንተ የሚወደኝ የለም ብትል እንኳን አንተን በማጣት የሚጎዱ ብዙ ሰዎች አሉ።

ህይዎት ብዙ ሰርፕራይዝ አላት፣ በፎቶው ላይ የሚታየው እንሰሳ ለልደቱ ስጦታ ሲበረከትለት ያሳየው ደስታ ነው፣ አጂብ አትልም፣ እንሰሳ በሚደረግለት ትንሽ ነገር ስሜቱን
እንደዚህ ሲገልፅ፣ ታዲያ አንተ አላህ ስንት ነገር አድርጎልሀል። በብር ለውጥ ብትባል የማትቀይረው ብዙ ነገርን ለግሶሀል።

አዎ አሁንም ከሁሉ በላይ አዛኙና ሩህሩህ የሆነው ጌታህ አላህ ይወድሀል፣ ያንተን መመለስ፣ በህይወትህ ትደሰት ዘንድ ምህረቱን አስፍቶ ይጠብቅሀልና ተመለስ።

««ወደአላህም ሽሹ!!!!!»»
#አቡሀኒፋሙሀመድሰዒድ

Comments

comments