የዘንድሮ የሙስና ዘመቻ የብኣዴንን ተዛዝሎ የማለፍ ሰንሰለት የሰበረ ይመስላል። by ተስፋኪሮስ ሳህሌ

 

 

1: ኢህኣዴግ የፖለቲካ ችግር ሲነሳበት የሃይል ሚዛን ያገኘ ተቀናቃኙን ወገንን ያስወግዳል። ኣጠቃላይ የቀውሱ  ድምዳሜ በኢህኣዴግ ደረጃ ይሆንና ኣፈፃፀሙ ግና በኣባል ድርጅቶቹ በኩል እንዲሆን ይደረጋል። በዚህ መልኩ የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች በተለይ ላለፉት 16 ኣመታት በየጊዜው ሲታመሱ እና ሰዎቻቸው ሲያራግፉ ኖረዋል። የተሸነፈ ወገን ከኣባል ድርጅቶቹ ማሰናበት ብቻ ሳይሆን ሰበብ እየተፈለገ ወደ ወህኒ ይርዳል።

 

2:ይኸ ኣጠቃላይ ገፅታው ሆኖ  በኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች ኣንድ የተለየ ሁኔታ  ግን ኣለ። የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች ሲታመሱ ብኣዴን ግን ውስጡ ሳይናጋ እና ኣሸናፊ እና ተሸናፊ ወገን ሳይታወቅ ተዛዝሎ ያልፋል። መጥፎ ነው ለማለት ሳይሆን ከኢህኣዴግ ባህልና ኣካሄድ ያፈነገጠ ነው ለማለት ያህል ነው።

 

3: የብኣዴን ኣመራር “ኣሳልፎ መስጠት በታምራት ላይኔ ይብቃ” የሚል መሃላ ኣለው ይባላል። ለዚህም ነው ኢህኣዴግ እና ኣባል ድርጅቶቹ ሲናጡ በብኣዴን መንደር ግን ኮሽ ሳይል የሚያልፈው።

 

4: የኢህኣዴግና ኣባል ድርጅቶቹ ምንጠራዋች ከኣጠቃላይ ግምገማ እንጂ ከተጨባጭ መረጃ ስለማይነሳ  ብኣዴን ተከልሎ ለማለፍ ምቹ ሁኔታዎች የፈጠሩለት ይመስላል። ኣጠቃላይ ግምገማዎቹ  ወደ ግለሰብ ለማውረድ ተጨባጭ መረጃ ኣላገኘሁም ብሎ ማለፍ ይችላል። ለምሳሌ የብኣዴን ኣመራር ኣምና በቅማንት ህዝብ እና በኣማራ ክልል የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ የደረሰው ጉዳት በድርጅታችን ውስጥ  የትምክህት ኣስተሳሰብ የበላይነት ስለተቀዳጀ ነው የሚል ድምዳሜ ኣስቀምጧል። ነገር ግን ግምገማውና ድምዳሜው ተከትሎ ሃላፊነት እንዲወስድና ተጠያቄ እንዲሆን የተደረገ ኣካል የለም።

 

5: ኣሁን ግን የብኣዴን ሰንሰለት የሚገዘግዝ መጋዝ የተገኘ ይመስላል_የኦዲት ሪፖርት። ብኣዴን ውስጥ የመሸገው ሃይል እንቅስቃሴው ፌዴራላዊ ስርኣቱ: ህወሓት እና የትግራይ ህዝብን ኢላማ ማድረጉ ህወሓትን በጣም,ሳያበሳጭ ኣልቀረም። ህወሓት በህልውናው የሚደራደር ኣይመስልም። ስለዚህ ኣጠቃላይ ግምገማው ብኣዴን ላይ ለውጥ የማያመጣ ከሆነ የፖለቲካው መንገድ በመተው ህግ እና መንግስታዊ ኣሰራርን መከተል የተመረጠ ይመስላል። ይቺ መንገድ ለብኣዴን የተመቸችው ኣትመስልም። ለዚህም ይመስላል የሙስናው ዘመቻ ይቁም የሚል ድምፅ ከዛ መንደር መናፈስ የጀመረው። ለህወሓት ደግሞ ከኣስቸኳይ ኣዋጁ ቀጥሎ ሞራል የሰጠው ይመስላል።

 

6: ብኣዴን መንግስታዊ መዋቅር ውስጥ ያለው የሙስና መዋቅሩ ብቻ ሳይሆን ሲያቀብጠው የትግራይን የኢኮኖሚ ኣከርካሪ ለመስበር በትግራይ ተወላጅ ባለሃብቶች ላይ የፈፀመው ክትትልና ኣሻጥር ኣጠቃላይ የኣገሪቱ የቢዝነስ ኣካሄድና የብድር ኣሰጣጥ,ስርኣቱ እንዲጠና እና እንዲጋለጥ መንገድ ከፍቷል። ኣሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል እንዲሉ ውጤቱ ደግሞ ለብኣዴን ሰዎች መልካም ዜና ይዞ የመጣ ኣይመስልም። የህወሓት ካድሬዎች ከመከላከል  ወደ ኣጥቂነት ያሸጋገረ ሂደት የተፈጠረ ይመስላል። ብኣዴን በቀደደው መንገድ የኣገሪቱ ገንዘብ (የባንክ ብድር) በማን እጅ እንዳለ ለማወቅ የተቻለ ይመስላል። ሰሞኑ  እየተነሳ ያለው የኣንድ ባለሃብት  የ6ቢልዮን የባንክ ብድርም የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ ላይሆን ይችላል።

 

7: የዘንድሮ የሙስና ዘመቻ የብኣዴን ሰዎችን ሰለባ በማድረጉ ወይም ደግሞ ኢህኣዴግ ብልሽቴ ከላይ ከከፍተኛ ኣመራሩ ነው የሚመነጨው እያለ የበታች ሹማምንቶችን ኢላማ በማድረጉ ሳይሆን ቢያንስ ከኣጠቃላይ ፖለቲካዊ ግምገማ ወጥቶ ተጠያቂነት በግልፅ ሊያስከትል ወደሚችል ወደ መንግስታዊ የፋይናንስ  ኣሰራር እና የኦዲት ሪፖርት መውረዱ ኣንድ እርምጃ ወደፊት የሄደ ነው የሚል ስሜት ኣለኝ። ብኣዴኖች ደግሞ ቻሉት እንግዲህ_ ድሮ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ ብላየ የለ ሴትየዋ።

Comments

comments