መንግስት በሙስና የተጠረጠሩ ከ30 በላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እና ነጋዴዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 18፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግስት በሙስና የተጠረጠሩ ከ30 በላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ ደላሎች እና ነጋዴዎችን ዛሬ በቁጥጥር ስር አውሏል።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፥ መንግስት ከሙስና ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በዋሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ግለሰቦች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው 31 ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ ደላሎች እና ነጋዴዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተናግረዋል።

የስራ ሀላፊዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉባቸው የመንግስት ተቋማትም የፌደራል እና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር እና ሌሎች ናቸው ተብሏል።

ሚኒስትሩ መንግስት ለህዝቡ በገባው ቃል መሰረት ከተሰጣቸው ሃላፊነት ውጭ ለልማት መዋል የነበረበትን የህዝብ ሃብት በማጉደል ወንጀል የተጠረጠሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ላይ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል።

ከፌደራል አቃቢ ህግ እና ፌደራል ፖሊስ በተውጣጣ ግብረ ሃይል በተደረገው ጥናትና ክትትል መሰረት፥ መረጃ የተገኘባቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋል ተጀምሯል ነው ያሉት።

በዛሬው እለት በቁጥጥር ስር ከዋሉት በተጨማሪም መረጃ የተገኘባቸው የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ባለሃብቶችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባር ይቀጥላል ብለዋል ሚኒስትሩ።

ሰፊ ጥናት እና ዝግጅት ሲደረግበት ቆይቶ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

መንግስት እስካሁን ለህብረተሰቡ ቃል ሲገባ የነበረውና በተደጋጋሚ ሲገለፅ የነበረው የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት እርምጃ በከፍተኛ ደረጃ መጀመሩን የሚያመላክት ነው የተባለው ይህ
ኦፕሬሽን በቀጣይ ቀናትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ታውቋል።

በዛሬው እለት በቁጥጥር ስር የዋሉት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ ደላሎች እና ነጋዴዎች ማንነት፣ ተሳተፉበት የተባለው የተባለው የወንጀል መጠን እና የወንጀል አይነትን መንግስት በቀናት ወሰጥ ይፋ እንደሚያደርግም በመግለጫው ተጠቅሷል።

Comments

comments