46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጠናቀቀ

ከግንቦት 8 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።

የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ መከላከያ ስፖርት ክለብ ሲሆን በሻምፒዮናው በ10 ስፖርቶች አዲስ ክብረ ወሰን ተመዝግበዋል፡፡

በዚህ ሻምፒዮና በ5 ሺህ ሜትር ሴቶች አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ አዲስ ክበረ ወሰን በማስመዝገብ ማሸነፍ ችላለች።

አትሌቷ 15 ደቂቃ ከ12 ሴኮንድ 16 ማይክሮ ሴኮንድ በሆነ ሰዓት በመግባት ነው ክብረ ወሰኑን ያስመዘገበችው።

አትሌት ሰንበሬ በ1997 ዓ.ም በአትሌት ገለቴ ቡርቃ 15 ደቂቃ ከ39 ሴኮንድ 12 ማይክሮ ሴኮንድ ተይዞ የነበረውን ሰዓት በ25 ሴኮንድ ለማሻሻል መቻሏን ነው ውጤቱ የሚያሳየው።

እንዲሁም በሴቶች የ1 ሺህ 500 ሜትር፣ በመሰናክል፣ በስሉዝ ዝላይ፣ በጦር ውርወራና በ20 ኪሎ ሜትር እርምጃ ውድድሮች አዲስ ክብረ ወሰን ሲመዘገብ፥ በወንዶች በኩል ደግሞ በምርኩዝና በስሉዝ ዝላዮች አዲስ ክብረ ወሰን መመዝገብ ችሏል።

በተጨማሪም በወንዶች በ1 ሺህ 500 ሜትር ሩጫ ከ17 ዓመት በፊት ጀምሮ በአትሌት ኃይሌ ገብረ ስላሴ ተይዞ የቆየው ክብረ ወሰን ተጋሪ አግኝቷል።

ከኦሮሚያ ክልል የመጣው አትሌት ተሬሣ ቶሎሣ 3 ደቂቃ 37 ሴኮንድ 90 ማይክሮ ሴኮንድ በማስመዝገብ ነው ክብረ ወሰኑን መጋራት የቻለው።

አትሌት ኃይሌም በዚህ ውድድር አዲስ ክብረ ወሰን ላስመዘገቡ አትሌቶች፥ በግሉ ለእያንዳዳቸው 10 ሺህ ብር ሽልማት አበርክቷል።

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዲስ ክበረ ወሰን ላስመዘገቡት አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው 10 ሺ ብር ሸልሟል።

በ46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻፒዮና አጠቃላይ አሸናፊ መከላከያ ስፖርት ክለብ ሲሆን፥ ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው ያጠናቀቁት ደግሞ ኦሮሚያ ክልልና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ናቸው።

በዚህ ሻምፒዮና ክስተት የነበረችው የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ አትሌት አርያት ዲቦ፥ በስሉዝ፣ በከፍታና በርዝመት ዝላዮች ሶስት ወርቆችን በማምጣት የውድድሩ ኮከብ አትሌት መሆን ችላለች።

አትሌቷ ሶስት ወርቅ ማምጣቷ ብቻ ሳይሆን በስሉዝና በከፍታ ዝላዮች ላይ አዲስ ክብረወሰን በማስመዝገብ ጭምር ነው ባለድል መሆን የቻለችው።

በዚህ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ800 ሜትር ጀምሮ እስከ 10 ሺህ ሜትር አሸናፊ የሆኑ አትሌቶች፥ ለንደን ላይ በሚካሄደው 16ኛው የዓለም ሻምፒዮና ለመሳተፍ በእጩነት ተመርጠዋል።

አትሌቶቹ የተሻለ ሰዓት ይመጣበታል ተብሎ በሚታሰበው ኒዘርላንድ ሄንጌሎ ላይ እርስ በእርስ የሚወዳደሩ ሲሆን፥ አሸናፊ የሆኑና ሚኒማውን የሚያሟሉ አትሌቶች በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሀገራቸውን ወክለው ይወዳደራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Comments

comments