ተቋማት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አሳሰበ

ኢትዮጵያን ጨምሮ በ150 አገራት የተከሰተውና ዲክሪፕት ዎነክራይ በመባል የሚታወቀው የሳይበር ጥቃት ኢላማ ያደረጋቸው ተቋማት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አሳሰበ፡፡በኢትዮጵያ ጥቃቱ ኢላማ ካደረጋቸው መካከል የቴሌኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማት፤ የገንዘብና ፋይናንስ፤ የኤሌክትሪክና ኢንዱስትሪ መቆጣጠሪያ ስርዓትና የኤም አር አይ ባለቤት የሆኑ ሆስፒታሎች ዋነኞቹ ናቸው፡፡

የደህንነት ስጋቱ ተጋላጭነት የሚስፋፋው በዊንዶው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ክፍተት አማካኝነት እንደሆነ መታወቁንም ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡

በመሆኑም የደህንነት ክፍተቱን ለመሙላትና ተቋማቱ ከተጋላጭነት ለመዳን ፕሮግራሙን ማደስ ወይንም አፕዴት ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝቧል፡፡

ማንኛውም ስጋቶች ሲያጋጥማቸው በ933 ወይም ethiocerty.insa.gov.et መልዕክት በመላክ አስፈላጊውን ድጋፍ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እንደሚያገኙ ተቋሙ አስታውቋል፡፡

Comments

comments