በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ቀንሷል

ከ100 ሺህ እናቶች 1 ሺህ 200 ያህሉን በወሊድ ሞት በማጣት የምትታወቀው ኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ እየጻፈች ነው።

ቀደም ባለው ጊዜ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወላጅ እናቶች፥ ልጃቸውን ያለ ህክምና ድጋፍ በቤት ውስጥ በልምድ አዋላጅ ይገላገሉ ነበር።

በዚህ ሳቢያም በተለይም ከከተማ ርቀው የሚኖሩ በርካታ እናቶች በወሊድ ምክንያት ህይወታቸውን ሲያጡ፥ የሚወለዱት ህጻናት ህይወትም ለአደጋ ይጋለጥ እንደነበር አስተያየታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሰጡ እናቶች ይናገራሉ።

አሁን ላይ የጤና ተቋማት በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቱ፥ ለወሊድ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ የሚፈልጉ እናቶችን ጉዞ በማሳጠር ለእናቶች ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ህብረተሰብም እፎይታን አስገኝቷል።

ከዚህ ባለፈም እንደ ቀደመው ጊዜ በቃሬዛ ተሸክሞ የሚደረገውን ጉዞ ለማሳጠር የአምቡላንስ አገልግሎት አሁን ላይ በተሻለ መልኩ ይገኛል።

አንዳንድ እናቶች በባለሙያ እንክብካቤ የሚወልዱባቸው ተቋማት የመስፋፋታቸውን ያህል በጤና ተቋማት መውለድን በቤት ውስጥ ቢወልዱ የሚደረግላቸውን ባህላዊ ስነ ሥርዓት እንደሚያስቀረው በመስጋት፥ ወደ ጤና ተቋማት ከመሄድ በመቆጠብ ዛሬም በቤት ውስጥ የመውለድ ፍላጎት አላቸው።

በርካታ የጤና ተቋማት ራቅ ወዳለ አካባቢ ለምትኖር እናት በጤና ተቋም የምትወልድበትን መቆያ ጨምሮ፥ በወሊድ ወቅት የሚከወኑ ባህላዊ ስነ ሥርዓቶችን ለማከናወን የሚያስችሉ ዝግጅቶችን ማሟላት ችለዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን በራያ ቆቦ ወረዳ የሚኖሩ እናቶችም በጤና ተቋማቱ የተተገበረው የወሊድ ስነስርዓት፥ ለእናቶችም ሆነ ለአካባቢው ህብረተሰብ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮ ችግሩ መቀረፉን ተናግረዋል።

ይህ ደግሞ የጨቅላ ህጻናትን እና የእናቶችን ሞት በመቀነስ እንደ ሀገር ትውልድን እየታደገ ያለ መንገድ ነው።

ሆኖም የህክምና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና የህክምና ባለሙያዎች የስነ ምግባር ጉድለት፥ በተመዘገበው ስኬት ላይ ክፍተት የሚፈጥር መሆኑን ተገልጋዮች ያነሳሉ።

እናቶች በወሊድ ምክንያት ህይወታቸውን እንዳያጡ አቋም ተይዞ ቢሰራም፥ አንዳንድ ባለሙያዎች የሙያ ግዴታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ጉዳቶች ሲከሰቱ ይስተዋላል፡፡

ይህን ለማስተካከልም አስተዳደራዊ እርምጃና መነሻውን ከስልጠና ተቋማቱ ያደረገ ስራ እየተሰራ ይገኛል።

ባለፉት 26 ዓመታት የእናቶች በጤና ተቋማት የመውለድ ሽፋን 70 በመቶ የደረሰ ሲሆን፥ አሁን ላይ ከ100 ሺህ እናቶች መካከል በ412 ላይ ሞት ይከሰታል።

ይህም ከዚህ ቀደም በወሊድ ወቅት ይመዘገብ ከነበረው 1 ሺህ 200 የእናቶች ሞት በእጅጉ ያነሰ ነው።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አህመድ ኢማኖ ባለፉት ዓመታት በጤናው መስክ የተመዘገቡ ስኬቶች የጤና ፖሊሲው ውጤታማነት መገለጫ ነው ይላሉ።

Comments

comments