በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኤስፔራንስ አቻ ተለያይቷል

በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ድልድል ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ ከተሞች ተካሂደዋል።

ኢትዮጵያን ወክሎ የሚወዳደረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቱኒዚያው ኤስፔራንስ ጋር ጨዋታውን አድርጓል።

10 ሰዓት ላይ የተደረገውን ጨዋታ ፈረሰኞቹ ያለምንም ጎል በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።

በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ የተሻለ የተንቀሳቀሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያገኟቸውን የጎል እድሎች መጠቀም አልቻሉም።

ኤስፔራንስ በ64ኛው ደቂቃ ላይ አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ ከሜዳ ቢወጣበትም፥ ጨዋታውን በአቻ ውጤት መጨረስ ችሏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመሪያው ጨዋታ ከአምናው የውድድሩ አሸናፊ ሰንዳውንስ ጋር ከሜዳው ውጭ አቻ መለያየቱ ይታወሳል።

በአንጻሩ የቱኒዚያው ተወካይ ክለብ ቪታን በሜዳው አስተናግዶ 3 ለ 1 ማሸነፉ ይታወሳል።

ውጤቱን ተከትሎም ኤስፔራንስ ምድቡን በአራት ነጥብ ሲመራ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለት ይከተላል።

በሌላ ጨዋታ የሞዛምቢኩ ፌሮቪያሪዮ ቤራ ከሱዳኑ አልሃሊ ኦምዱርማን በተመሳሳይ ውጤት ያለምንም ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

Comments

comments